አዋጅ ቁጥር 232/2008 ዓ.ም

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአካባቢ፣ የደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣንን ለማቋቋም የወጣ አዋጅ

ሁሉን አቀፍ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ዘላቂነት ላለው የክልሉ ልማት መሰረት እንደሆነ የታመነ በመሆኑ፤

በክልሉ የተፈጥሮ ሁብት ልየታና እንክብካቤ ላይ አተኩረው የሚፈፀሙትን የአካባቢ ጥበቃና የደን ልማት ስራዎች በተማከለ መንገድ ማስተባበርና በሣይንሳዊ እውቀት ላይ ተመስርቶ መምራት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤

በክልሉ ውስጥ የሚገኙትን የአካባቢ ሀብቶች በሚገባና ዘለቄታ ባለው መንገድ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ አካባቢን የሚጐዱ ወይም የሚበክሉ ተግባራትን መከታተል፣ መመርመር፣ መቆጣጠርና ጥፋት ተፈፅሞ ሲገኝ የእርምት እርምጃዎችን መውሰድ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፤

ለዚሁ ያመች ዘንድ በክልሉ ውስጥ የአካባቢ እንክብካቤና የደን ልማት እንቅስቃሴዎች በተመለከተ ራሱን የቻለና ተጠያቂነት ያለው አስፈፃሚ መስሪያ ቤት በህግ ማቋቋምና ስልጣንና ተግባራቱን በዝርዝር መደንገግ በማስፈለጉ፤

የአማራ ክልል ምክር ቤት በተሻሻለው የብሄራዊ ክልሉ ህገ-መንግስት አንቀጽ /49/ ንዑስ አንቀፅ 3/1/ ድንጋጌ ስር በተሰጠው ስልጣን መሠረት ይህንን አዋጅ አውጥቷል፡፡

ክፍል አንድ

ጠቅላላ ድንጋጌዎች

 1. አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅ "የአካባቢ፣ የደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 232/2008 ዓ.ም"  ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

 1. ትርጓሜ

የቃሉ አግባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ፡-

 1. "አግባብ ያለው መሥሪያ ቤት" ማለት ቃሉ የተጠቀሰበት ድንጋጌ በሚመለከተው ጉዳይ ላይ በህግ የተሰጠ ኃላፊነት ያለው የክልሉ ወይም የፌዴራል መንግስት ተቋም ነው፣
 2. "አካባቢ" ማለት በመሬት፣ በከባቢ አየር፣ በአየር ሁኔታ እና በአየር ንብረት፣ በውሃ፣ በሕያዋን፣ በድምጽ፣ በሽታ፣ በጣዕም፣ በማህበራዊ ጉዳዮች እና በሥነ ውበት ሣይወሰን፣ በተፈጥሮአዊ ሁኔታቸው ወይም በሰው አማካኝነት ተሻሻለው ወይም ተለውጠው የሚገኙ ነገሮች በሙሉ ያሉበት ቦታ፣ እንዲሁም መጠናቸውን ወይም ሁኔታቸውን ወይም ደግሞ የሰው ወይም የሌሎች ሕያዋን በጎ ሁኔታን የሚነኩ ተስታጋብሮዎቻቸው ድምር ነው፤
 3. "አደገኛ ነገር" ማለት በሰው ጤና ወይም በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ጠጣር፣ ፈሳሽ ወይም የጋዝነት ባህርይ ያለው ነገር ወይም ተክል፣ እንስሳ ወይም ረቂቅ ሕዋስ ነው፣
 4. "ጥበቃ" ማለት የተፈጥሮ ባህርይ እንዳይናጋ በመጠበቅና የተፈጥሮ ሀብቶች ምንጭ አቅምን በማጎልበት የአሁኑን ትውልድ ፍላጎት የማርካቱ ሂደት የመጪውን ትውልድ ዕድል ሣያሰናክል እንዲሟላ ማስቻል ነው፡
 5. "የመንግስት ደን" ማለት በክልሉ መንግስት ባለቤትነት ስር የዋለ ማናቸውም ጥብቅ ወይም ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚውል ደን ነው፣
 6. "ሰው" ማለት የተፈጥሮ ሰው ወይም በህግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፡፡

ክፍል ሁለት

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስለ አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን መቋቋም፣ ዓላማ፣ ስልጣንና ድርጅታዊ አቋም

 1. መቋቋምና ተጠሪነት
 2. በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የአካባቢ፣ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ልማት ባለስልጣን ከዚህ በኃላ "ባለስልጣኑ" እየተባለ የሚጠራው ራሱን የቻለና ህጋዊ ሰውነት ያለው የክልሉ መንግስት አስፈፃሚ መስሪያ ቤት ሆኖ በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል፣
 3. የባለስልጣኑ ተጠሪነት ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጽ/ቤት ይሆናል፡፡
 1. ዓላማዎች

ባለስልጣኑ በዚህ አዋጅ መሠረት የሚከተሉት ዓላማዎች ይኖሩታል፡-

 1. በክልሉ ውስጥ የሚከናወኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንስቃሴዎች የሰውን በጐ ሁኔታና የአካባቢን ደህንነት በዘላቂነት ለማራመድ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ፣ ህጐችንና ስልቶችን ማዘጋጀትና ውጤታማነታቸውን ለማረጋገጥ የሚከናወነውን ተግባር በግንባር ቀደምትነት መምራት፤ እና
 2. በክልሉ ውስጥ የሚገኙትን ከፍተኛ የመንግስት ደኖች መጠበቅ፣ ማልማትና ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲውሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፡፡
  1. ዋና መስሪያ ቤት

የባለስልጣኑ ዋና መስሪያ ቤት በባህር ዳር ከተማ ውስጥ ሲሆን በክልሉ ውስጥ በሌሎች ስፍራዎች እንደ አስፈላጊነቱ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን ሊያቋቁም ይችላል፡፡

 1. የባለስልጣኑ ስልጣንና ተግባር

ባለስልጣኑ ዓላማዎቹን ከግብ ለማድረስ የሚከተሉት ዝርዝር ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-

 1. በክልሉም ሆነ በፌደራሉ ህግጋተ-መንግስታት የተደነገጉ የአካባቢ ደህንነት ዓላማዎችና በሀገሪቱ የአካባቢ ፖሊሲ ውስጥ የሰፈሩት መሠረታዊ መርሆዎች ከግብ መድረሳቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን ያስተባብራል፣
 2. አግባብ ካላቸው መስሪያ ቤቶች፣ ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላትና ከነዋሪው ህዝብ ጋር በመመካከር ረቂቅ የአካባቢ ፖሊሲ ማስፈፀሚያ ህጐችን፣ መርሀ-ግብሮችንና ስልቶችን ያዘጋጃል፣ ይገመግማል፣ ይቆጣጠራል፣
 3. የአካባቢን ደህንነት ለመጠበቅ ወይም በማናቸውም ሁኔታ የተጎዳ ወይም የተጐሳቆለ አካባቢን መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ አግባብ ካላቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር ግንኙነቶችን ይፈጥራል፣ እንደአስፈላጊነቱ የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ይሰጣል፣
 4. በመንግስትም ሆነ በግል ፕሮጀክቶች፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ የልማት ፖሊሲዎች፣ ስልቶች፣ ህጎችና መርሃ ግብሮች ላይ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ለማካሄድ የሚያስችል ክልል አቀፍ ሥርዓት ይዘረጋል
 5. አግባብ ካላቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር በተመባበር በክልሉ ውስጥ በረሀማነትን ለመከላከልና የድርቅን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚያስችሉ ጥናቶችን ያካሂዳል፣ መፍትሔዎችን ያዘጋጃል፣ ለአተገባበራቸውም ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል
 6. በልማት እቅዶችና በኢንቨስትመንት መርሃ ግብሮች ውስጥ የሚካተቱ የአካባቢ የአዋጪነት ማስሊያ ቀመሮችንና የስሌት ሥርዓትን አግባብ ካላቸው መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጃል ወይም እንዲዘጋጁ ያደርጋል፣ እንደሁኔታውም በጥቅም ላይ የመዋላቸውን ሂደት ይከታተላል
 7. ዘላቂነት የጎደለው የተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀምና ልምድን፣ የአካባቢ ጉስቁልናን ወይም ብክለትን ለመከላከል በሚያስችሉ የመግቻ እርምጃዎች ወይም የማበረታቻ ዘዴዎች መጠቀምን በተመለከተ አግባብ ካላቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር በመመካከር ሃሣብ ያቀርባል
 8. አግባብ ካላቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር በመመካከር የአካባቢ መረጃ አሰባሰብን፣ አደረጃጀትንና አጠቃቀምን የሚያቀላጥፍ ሥርዓት ይዘረጋል፣ በስራ ላይ እንዲውል  ያደርጋል
 9. የአካባቢ ጥበቃና የደን ልማት ምርምሮችን ያስተባብራል፣ ያበረታታል፣ እንደአስፈላጊነቱም ራሱ ያካሂዳል፤
 10. አግባብ ባላቸው የህግ ድንጋጌዎች መሠረት የአካባቢ ጥበቃ ግዴታዎች መከበራቸውን ለማረጋገጥ በገጠርም ሆነ በከተማ አስተዳደር ሥልጣን ሥር ወደሚገኝ ማናቸውም መሬት፣ ቅጥር ግቢ ወይም ሌላ ቦታ ይገባል፣ ኃላፊነቱን ለመወጣት ተገቢ ሆኖ ያገኘውን ማንኛውንም ነገር ይፈትሻል፣ ናሙናዎችን ይወስዳል፤
 11. የክልሉን የአካባቢ ሁኔታ ዘገባ በየወቅቱ እያዘጋጀ ለመንግስትም ሆነ ለህዝብ እንዲደርስ ወይም እንዲሰራጭ ያደርጋል፤
 12. መደበኛ ያልሆኑ የአካባቢ ትምህርት መርሃ ግብሮችን ያስፋፋል፣ ትምህርቱን ይሰጣል፣ አካባቢያዊ ጉዳዮችን በመደበኛ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ለማካተት አግባብ ካላቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር ትብብር ያደርጋል፤
 13. የአካባቢ ጥበቃ የድርጊት እቅዶችንና ፕሮጀክቶችን ዝግጅት ያበረታታል ወይም ያግዛል፣ ለድርጊት ዕቅዶቹና ፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ የሚውሉ እገዛዎችን ያፈላልጋል፤
 14. ሀገር አቀፍ የአካባቢ ደህንነት፣ የደንና የዱር እንስሳት ጥበቃ፣ ልማትና አጠቃቀም ህጎችን በክልሉ ውስጥ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስፈልጉትን መመሪያዎች ያወጣል፣ በተግባር ላይ አንዲውል ያደርጋል፤
 15. የአካባቢ አያያዝንና ጥበቃን ተቀዳሚ ዓላማው በማድረግ ለሚሰራ ለማናቸውም ድርጅት ወይም ግለሰብ ምክር እንዲሁም የሚቻል ሲሆንና የአካባቢ ምክር ቤቱ ሲስማማበት የፋይናንስ ወይም የቴክኒክ ድጋፎችን ይሰጣል፤
 16. አግባብ ያላቸው መስሪያ ቤቶች በዚህ አዋጅና በሌሎች ህጎች የተጣሉባቸውን ኃላፊነቶች በሚወጡበት ሁኔታ ላይ ተገቢውን የምክር አገልግሎት ይሰጣል፣ እንደአስፈላጊነቱም እርምት ሊወሰድባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ለክልሉ መንግስት የውሳኔ ሀሣብ ያቀርባል፤
 17. በአካባቢ ላይ የሚደርሱ ድንገተኛ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ለመቋቋም ስለሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች የክልሉን መንግስት ያማክራል፤
 18. የክልሉን የአካባቢ ጥበቃና የደን ይዞታ በሚመለከቱ ጉዳዮች አግባብ ላላቸው አካላት ስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ይሰጣል፤
 19. በክልሉ ውስጥ የሚካሄደውን የደን ሀብት ውጤቶች ዝውውር ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፤
 20. የክልሉ ህብረተሰብ በዱር እንስሳት አያያዝ፣ ልማትና አጠቃቀም ረገድ በቂ ግንዛቤ ሊያገኝ የሚችልበትን ስልት ይቀይሳል፣ በሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፣ ብርቅየ የዱር እንስሳት ዝርያዎች ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤
 21. አግባብ ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ወንዞችንና ሀይቆችን የሚያዋስኑ አካባቢዎችን እንዲሁም እርጥበት አዘል መሬቶችን ረግረጋማ ስፍራዎችን ደህንነት ይጠብቃል፣ ይንከባከባል፤
 22. የብዝሀ-ህይወት፣ የስርዓተ-ምህዳሮችንና የሌሎች የአካባቢ ሀብቶችን አያያዝ፣ አጠቃቀምና ልማት ለማሻሻል የሚያግዙ ጥናቶችን ያካሂዳል፣ በጥናቱ ለተለዩ ችግሮች የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የመፍትሄ እርምጃዎችን ይወስዳል፣
 23. የአካባቢ ሀብቶችን አስመልክቶ የዋጋ ትመና ጥናቶችን ያካሂዳል፣ በትመናው ውጤት መሠረትም ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ሲነደፉ በአዋጪነት ስሌታቸው ውስጥ የአካባቢ ሀብቶች ዋጋ እንዲካተት ያደርጋል፣ በትግበራ ወቅት ለሚደርሰው ማናቸውም የአካባቢ ሀብት ጥፋት በሀብት ትመናው መሠረት ተመጣጣኝ ካሣ እንዲከፈል ያደርጋል፤
 24. የአካባቢ ደህንነት ለማስከበር ስልጣን፣ ኃላፊነትና ተግባር በተሰጣቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ተግባር ላይ የምርመራና የክትትል ስራዎችን ያከናውናል፣ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡት ላይ ደግሞ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ያደረጋል፤
 25. የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማዎችን ለማካሄድ የሚያስችሉ ስልቶችን ይቀይሳል፣ ሪፖርቶችን በመርመር የእርምትና የማስተካከያ አስተያየቶችን ይሰጣል፣ ተስተካክለው በቀረቡ ሰነዶች አንፃር የይሁንታ ፈቃድ ይሰጣል፤
 26. ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በክልሉ ውስጥ የሚገኙትን ከፍተኛ የመንግስት ደኖች፣ ፖርኮችና ሌሎች ጥብቅ ስፍራዎች ያጠናል፣ ይከልላል፣ ይመዘግባል፣ ያስተዳድራል፣ ያለማል፤ በሌሎች እንዲለሙ ያደርጋል፤
 27. የንብረት ባለቤት ይሆናል፣ውል ይዋዋላል፣በስሙ ይከሳል፣ይከሰሳል፤
 28. ዓላማዎቹን ለማሳካት አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ተዛማጅ ተግባራትን ያከናውናል፡፡
 29. ድርጅታዊ አቋም

ባለስልጣኑ በዚህ አዋጅ መሠረት የሚከተሉት አካላት ይኖሩታል፡-

 1. የአካባቢ ምክር ቤት ከዚህ በኃላ "ምክር ቤቱ" እየተባለ የሚጠራ፤
 2. በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አማካኝነት የሚሾሙ ዋና ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጆች፤
 3. ለስራው የሚያስፈልጉ የበታች ስራ ሀላፊዎችና ሙያተኞች፡፡
 4. ስለ ምክር ቤቱ አባላት ተዋፅኦና ጥንቅር

ምክር ቤቱ በዚህ አዋጅ መሠረት ከሚከተሉት የተውጣጣ ይሆናል፡-

 1. በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚሰየም ከፍተኛ የስራ ሀላፊ  ሰብሳቢ፤
 2. በርዕስ መስተዳድሩ ተመርጠው የሚሰየሙና የተለያዩ መንግስታዊ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ሀላፊዎች  አባላት፤
 3. የዞን ዋና አስተዳዳሪዎችና የሜትሮፖሊታን ከተማ አስተዳደሮች ከንቲባዎች  አባላት፤
 4. የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ተወካይ  አባል፤
 5. በአካባቢ አያያዝና እንክብካቤ ስራ ላይ የተሰማሩ ክልል በቀል የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተወካይ  አባል፤
 6. የክልሉ ሠራተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ተወካይ  አባል፤
 7. የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ  አባልና ፀሐፊ፤    
 8. የምክር ቤቱ ስልጣንና ተግባር

ምክር ቤቱ በዚህ አዋጅ መሠረት የሚከተሉት ዝርዝር ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-

 1. የሀገሪቱን የአካባቢ ፖሊሲ ክልል አቀፍ ተፈፃሚነት አስመልክቶ ባለሥልጣኑ በሚያቀርበው ዘገባ መሠረት ግምገማዎችን ያካሂዳል፣ አቅጣጫዎችን ይሰጣል
 2. በባለስልጣኑ ስራ አመራር በኩል ተዘጋጅተው የሚቀርቡለትን ረቂቅ አካባቢ ነክ ፖሊሲዎች፣ ህጐችና ስልቶች ይመረምራል፣ ለክልሉ መንግስት የውሳኔ ሀሣቦችን ያቀርባል
 3. በባለሥልጣኑ ተዘጋጅተው የሚቀርቡለትን ረቂቅ የማስፈፀሚያ መመሪያወች  መርምሮ ያፀድቃል፡፡
 4. ስለ ምክር ቤቱ የስብሰባ ጊዜና የውሣኔ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት
  1. ምክር ቤቱ በስድስት ወር አንድ ጊዜ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄዳል፣ ሆኖም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በማናቸውም ጊዜ አስቸኳይ ስብሰባዎች ሊያካሂድ ይችላል፤
  2. በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ አብላጫ ቁጥር ያላቸው አባላት ከተገኙ ምልዓተ-ጉባኤ ይሆናል፤
  3. የምክር ቤቱ ውሣኔዎች በድምፅ ብልጫ ያልፋሉ፣ ሆናም ድምፁ እኩል ለእኩል የተከፈለ እንደሆነ ስብሰባው የደገፈው ሀሣብ የምክር ቤቱ ውሣኔ ይሆናል፤
  4. የዚህ አንቀጽ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ምክር ቤቱ የራሱን ዝርዝር የስብሰባ ጊዜና የውሳኔ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ደንብ ሊያወጣ ይችላል፡፡
  1. የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚሾም ሲሆን ተጠሪነቱም ለምክር ቤቱና ለዚሁ አካል ይሆናል፤
  2. የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚሾም ሲሆን ተጠሪነቱ ለዋና ስራ አስኪያጅ ይሆናል፡፡
  1. ዋና ስራ አስኪያጅ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመሆን የባለሥልጣኑን ሥራዎች በበላይነት ይመራል፣ ያስተባብራል፤
  2. የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቅጽ/1/ አጠቃላይ ድንጋጌ አንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ፡-

ሀ/ በክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ህጐች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መሠረት የባለሥልጣኑን

   ሠራተኞች ይቀጥራል፣ ያስተዳድራል፣ ያሳድጋል፣ ያሰናብታል፤

ለ/ የባለሥልጣኑን የሥራ ፕሮግራምና በጀት ያዘጋጃል፣ ሲፈቀድም በሥራ ላይ

   ያውላል፤

ሐ/ ለባለሥልጣኑ በተፈቀደለት በጀትና የሥራ መርሃ ግብር መሠረት ገንዘብ ወጪ

    ያደርጋል፤

መ/ ከሶስተኛ ወገኖች ጋር በሚደረጉ ግነኙነቶች ባለሥልጣኑን ይወክላል፤

ሠ/ የባለሥልጣኑን ወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴና የፋይናንስ ዘገባዎች ለምክር ቤቱና ለርዕስ መስተዳድሩ ያቀርባል፤

ረ/ ለባለሥልጣኑ የሥራ ቅልጥፍና በሚያስፈልግ መጠን ከስልጣንና ተግባሩ ለበታች የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ሠራተኞች በውክልና ሊሰጥ ይችላል፡፡

 1. ስለ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ስልጣንና ተግባር

ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ከዋና ስራ አስኪያጅ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት፡-

 1. የባለሥልጣኑን ተግባሮች በማቀድ፣ በማደራጀት፣ በመምራትና በማስተባበር ዋና ሥራ አስኪያጁን ይረዳል፤
 2. በዋና ሥራ አስኪያጁ ተለይተው የሚጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል፡፡
 3. ዋና ስራ አስኪያጅ በማይኖርበት ወይም ስራውን ለማከናወን በማይችልበት ጊዜና ሁኔታ እርሱን ተክቶ ይሰራል፡፡

ክፍል ሶስት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

የባለስልጣኑ በጀት በክልሉ መንግስት ይመደባል፡፡

  1. ባለስልጣኑ የተሟሉና ትክክለኛ የሆኑ የሂሣብ መዛግብትን ይይዛል፤
  2. የባለስልጣኑ የሂሣብ መዛግብትና ገንዘብም ሆነ ንብረት ነክ ሰነዶች በክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በየጊዜው ይመረመራሉ፡፡

ይህንን አዋጅ የሚቃረን ማናቸውም ሌላ ህግ፣ ደንብ፣ መመሪያ ወይም የተለመደ አሠራር በዚህ አዋጅ ውስጥ በተሸፈኑት ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡

 1. መብቶችና ግዴታዎችን ስለማስተላለፍ

የአካባቢ ጥበቃንም ሆነ የመንግስት ደኖችና ፖርኮች ልማት ጉዳዮችን አስመልክቶ እንደየአግባብነቱ በአዋጅ ቁጥር 176/2003 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 181/2003 ዓ.ም ለክልሉ አካባቢ ጥበቃ፣ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም፣ ለግብርናና ለባህል ቱሪዝምና ፖርኮች ልማት ቢሮዎች ተሰጥተው የነበሩ መብቶችና ግዴታዎች በዚህ አዋጅ መሠረት አዲስ ወደ ተቋቋመው የክልሉ አካባቢ ጥበቃና የደን ልማት ባለስልጣን ተላልፈዋል፡፡

  1. የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች በተሟላ  ሁኔታ ለማስፈፀም የሚያስፈልጉትን ደንቦች ሊያወጣ ይችላል፤
  2. ምክር ቤቱ ይህንን አዋጅና በዚህ አዋጅ መሠረት የሚወጡትን ደንቦች በተሟላ ሁኔታ ለማስፈፀም የሚያስፈልጉትን ዝርዝር መመሪያዎች ሊያወጣ ይችላል፤

ይህ አዋጅ በክልሉ መንግስት ዝክረ -ህግ ጋዜጣ ታታሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

ባህር ዳር

ጥር 25 ቀን 2008 ዓ.ም

ገዱ አንዳርጋቸው

የአማራ ብሔራዊ ክልል ፕሬዚዳንት

Online Users

We have 3 guests online
About Service Delivery